እጅግ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው “የራንሰምዌር” ጥቃት | Ransomware attacks becoming a major concern
ከጥቂት ሳምንታንት በፊት በአሜሪካን የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈጸመ የራንሰምዌር ጥቃት ሳቢያ በሀሪቱ የነዳጅ አቅርቦት ስርዓት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል ፈጥሮ ሰንብቷል፡፡ የራንሰምዌር ጥቃቱ የአገሪቱን ትልቁን የነዳጅ ቧንቧ መስመር ከአገልግሎት ውጭ በማድረግ የአሜሪካ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ ሕግ እንዲያወጣ አስገድዷል፡፡
ይህ ጥቃት በአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ በርካታ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ ሲሆን ከነዚህም መካከል አቅራቢዎች በካምፓኒዎች ዘንድ ያላቸውን ተአማኒነት መልሰው ለማግኘት ረጅም ጊዜ ይወስድባቸዋል፡፡
የራንሰምዌር ጥቃቶች የሚሰነዘሩት በዋናነት በንግድ ሥራ በተሰማሩ አካላት ላይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህ የያዝነዉ የፈረንጆቹ 2021 በራንሰምዌር ጥቃት መላው ዓለም በተለይም የጤና ተቋማት ክፉኛ የተጠቁበት ዓመት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
የእነዚህ የራንሰምዌር ጥቃት አድራሾች ዋና አላማ የንግድ አገልግሎትን ማስተጓጎል ነው፡፡ ከዚህም ባለፈም ወሳኝ የሚባሉ አገልግሎት አቅራቢዎች በራንሰምዌር ጥቃት ፈጻሚዎች ዒላማ እይታ ውስጥ ናቸው ምክንያቱም በራንሰምዌር ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ላልተወሰነ ጊዜ የንግድ ሥራ ሂደቶች ሊቋረጡ ወይም ጥቃቱን የሰነዘረው አካል ለጠየቀው የራንሰም ክፍያ ከፍለው የተቋረጠውን አገልግሎት ወደማስመለስ ግዴታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡
በንግድ ሥራ ዉስጥ ላልተወሰነ ጊዜ አገልግሎትን ማቋረጥ እና መዝጋት ከፍተኛ ኪሳራን ስለሚያደርስ በአብዛኞቹ የጥቃት ሰለባዎች ዘንድ እንደመፍትሔ አይወሰድም፡፡ በመሆኑም አገልግሎት አቅራቢዎች ክፍያ ወደመፈፀም አማራጭ ብቻ ተገደው እንዲገቡ ያደርጋቸዋል፡፡
ስለዚህ የራንሰምዌር ጥቃቶችን ለመከላከል ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
በአብዛኛዉ የሳይበር ወንጀለኞች ገንዘብ ለማግኘት ቀላሉን መንገድ ይመርጣሉ፡፡ እንደማሳያም ሰሞኑን በአሜሪካ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር የኮምፒዉተር ስርዓት ላይ ጥቃት ያደረሱ አካላት "ዓላማችን ገንዘብ ማግኘት ነው" በማለት አሳውቀዋል፡፡
አደገኛ የሆኑ እና ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ የሚያደርሱ የራንሰምዌር ጥቃቶችን ለመቀነስ ምን ተግባራት መፈጸም ይኖርብናል የሚለዉን ከዚህ በታች እንደሚከተለዉ ይቀርባል፡-
1. ጠንካራ-የይለፍ-ቃል መጠቀም፡- በተቋማት ዉስጥ ጥቅም ላይ የሚዉሉ የይለፍ-ቃሎች “12345” እና መሰል ተገማች የሆኑ የይለፍ-ቃሎችን ሠራተኞች እንዳይጠቀሙ የይለፍ-ቃል ፖሊሲ በማዘጋጀት ተፈጻሚ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
2. መጠባበቂያ መያዝዎን ሁልጊዜ ማረጋገጥ፡ ወሳኝ እና ሚስጥራዊ የሆኑ መረጃዎችን ግልባጭ መያዝዎን እና መረጃዎቹ በአስተማማኝ ሁኔታ መኖራቸውን በየጊዜው ማረጋገጥ፡፡
3. ዓይነተ-ብዙ የደህንነት መጠበቂያ መጠቀም፡- ይህም የመረጃ በርባሪዎች በቀላሉ ወደ ኮምፒዉተር ስርዓታችን እንዳይገቡ እና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲኖሩ ማሳወቂያ አንድናገኝ ያስችለናል ፡፡
4. የተፈቀዱልንን አካውንቶች የይለፍ ቃል ደህንነት መጠበቅ፡- ወደ ተቋማት ስርዓተ ኮምፒዉተር እንድንገባ የተሰጠንን የይለፍ ቃል ደህንነት ማረጋገጥ እና የመረጃ በርባሪዎች የእኛን የይለፍ ቃል ተጠቅመዉ በተቋሙ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡
5. ወቅታዊ የሆኑ የሳይበር ደህንነት ዝመና እና ለሚፈጠሩ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ምላሽ መስጫ እቅድ ማዘጋጀት፡፡
6. በሳይበር ደህንነት እና ስጋቶች ዙሪያ ሁልጊዜም ጥንቁቅ እንዲሁም ንቁ መሆን፡፡
7. የሚጠቀሙበት መሣሪያ በየጊዜው ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ፡- የሚሰሩበት ተቋም ሶፍትዌሮችን እና የኦፕሬቲንግ ስርዓቶችን የሚፈተሽበትን ጊዜ ርዝመት ማሳጠር እና በየጊዜው የሚሆንበትን አግባብ ሊከተል ይገባል፡፡
8. ያልተለመዱ የኢ-ሜይል አባሪዎችን መዝጋት፡- ሠራተኞች መጨራሻቸው ላይ exe, .scr, .ps1, .vbs, የመሳሰሉ ያለባቸውን አባሪዎችን ከመክፈት መቆጠብ አለባቸው፡፡ በእርግጥ ማይክሮሶፍት በቀጥታ መሠል አባሪዎችን ሲያገኝ ያጠፋል፡፡ ነገር ግን አስፈላጊ ሲሆን በኢ-ሜይል የደህንነት መጠበቂያ ሥርዓት በልዩ ሁኔታ ፈቃድ እንዲቀበል በማድረግ ማስተናገድ ይቻላል፡፡
Source: Information Network Security Agency
Comments
Post a Comment
Nice To Hear From You we will be responsive as possible as we can. Thank you!!